አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም— ሴቶች የፋይናንስ ተጠቃሚነታቸው እንዲጨምርና በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ወደ አመራር እንዲመጡ ብሎም አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ለማስቻል አስተዋጽኦ የሚያደርግ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ባለሙያ ሴቶች ኔትዎርክ (ኒውፊን) በይፋ ተመሠረተ።
የኔትዎርኩ (ኒውፊን) መመሥረት በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ሴቶችን በአመራር ደረጃ የሚኖራቸውን ሥፍራና ሚና ለማጎልበት እንዲሁም በዘርፉ የሚታየውን የፆታ ተሳትፎ ልዩነት ለማጥበብና ባጠቃላይም በአገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት ላይ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አመቺ ምህዳር ለመፍጠር እንደሚያስችል ታምኖበታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሥራ ላይ ባዋለው ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ (ከ2021 – 25 እ.ኤ.አ) በፋይናንስ ተጠቃሚነት ረገድ በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን ልዩነት (ያልተመጣጠነ ተጠቃሚነት) ለማጥበብ ልዩ ልዩ ተግባራት ተከናውነዋል።
በዚህ የፋይናንስ አካታችነት መርሐግብር አበረታች ውጤቶች የተገኙ ቢሆንም፣ በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለው የተሳትፎና የተጠቃሚነት ድርሻ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሠፋ መጥቷል። ይህም በፋይናንስ ኢንዱስትሪው እንደ አንድ ትልቅ ክፍተት ሆኖ የሚመዘገብ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በፋይናንስ ተቋማት የሚሠሩ ሴቶች በበቂ ቁጥር ያህል ወደ አመራርነት እንዲመጡ ባለመደረጋቸው በአገር አቀፍ ደረጃ ሴቶች የዘርፉ ሙሉ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ለመገንዘብ ተችሏል።
በመሆኑም ለተጠቀሱትና ተያያዥ ተግዳሮቶች መፍትሔ መሥጠት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ለሥርዓተ ፆታ ትልቅ ትኩረት የሚሠጥ የፋይናንስ ዘርፍ ለመፍጠርና የአገሪቱ ቀዳሚ አጀንዳ የሆነውን የሴቶች የፋይናንስ አካታችነትን ከግብ ለማድረስ የኔትዎርኩ መመሥረት ትልቅ አስቻይ አደረጃጀት መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያምናል።
ሴቶችን ወደ አመራር ደረጃ የሚያሳድግ፣ በሁለንተናዊ መልኩ የሚያበቃና፣ የፆታ እኩልነትን የሚያሰፍን የፋይናንስ ዘርፍ ጎልብቶ ማየት የኒውፊን ራዕዮች ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኔትዎርኩ (ኒውፊን) እንዲመሠረት ያደረገው ከዓለም ባንክ ጋር በተመባበር በመተባበር ሲሆን፣ ኔትዎርኩ በአፍሪካ ውስጥ ቀደም ብሎ ሩዋንዳ ላይ ከተቋቋመው ተመሳሳይ ኔትዎርክ ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ አብሮ ለመሥራት መዘጋጀቱ ታውቋል።