ኒውፊን ወጣት ሴት የፋይናንስ ባለሙያዎችን አሰለጠነ!

Share the post

የኢትዮጵያ ሴት ፋይናንስ ባለሙያዎች ኔትዎርክ (NEWFin) ለወጣት ሴት የፋይናንስ ባለሙያዎች (YWPD) አቅም ለመገንባት ያዘጋጀውን ሥልጠና አጠናቅቆ አስመረቀ። ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው በዚህ የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ የባንክ ፕሬዚዳንቶች፣ የኒውፊን ቦርድ አባላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በሥልጠናው መርሐግብር ላይ ከ19 ባንኮች የተውጣጡ 302 ሠልጣኞች የተሳተፉ ሲሆን፣ ሠልጣኞቹም እ.ኤ.አ. በ2022፣ በ2023 እና በ2024 በየባንኮቻቸው የተቀጠሩ ወጣት ባለሙያዎች መሆናቸው ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ክቡር ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ በሥነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ሴት ፋይናንስ ባለሙያዎች ኔትዎርክ (NEWFin) በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል ወጣቶች አሠልጥኖ ለውጤት ማብቃቱ የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጸዋል። የዚህ የወጣት ሴት ባለሙያዎች አቅም ግንባታ ለምረቃው (YWPD) ተሳታፊ ሠልጣኞች በመድረሳቸው “እንኳን ደስ ያላችሁ!” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ አካታችነትን በሚገባ ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ ሴት ፋይናንስ ባለሙያዎች ኔትዎርክ (NEWFin) ትልቅ ድርሻ እንደሚወጣና በዚህ መርሐግብር ከወዲሁ እንዳስመሰከረ አመልክተዋል። በፋይናንስ ሴክተር ውስጥ የሴቶች ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የፋይናንስ ተቋማቱ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ያመለከቱት ክቡር ገዥ፣ ይህንን ጉዳይ የበለጠ ስኬታማ ለማድረግ ደግሞ ሴቶችን ወደ አመራር ማምጣትና በቦርድ አባልነት ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ሴት ፋይናንስ ባለሙያዎች ኔትዎርክ (NEWFin) በዚህ ረገድ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት የተቋቋመ አደረጃጀት በመሆኑ፣ በቀጣይ ኔትዎርኩ የሚሠጣቸውን ተመሳሳይ ሥልጠናዎች በሚገባ መጠቀም እንዲመገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሴት ፋይናንስ ባለሙያዎች ኔትዎርክ (NEWFin) ሊቀመንበር ወይዘሮ መሊካ በድሪ በበኩላቸው እንዳሉት የወጣት ሴት ባለሙያዎች አቅም ግንባታ መርሐግብር በባንክ ዘርፍ ውስጥ ወደፊት እንዲኖሩን የምንፈልጋቸውን ሴት መሪዎች ለማፍራት መሠረት የጣልንበት ትልቅ ፕሮጀክት ነው። ሥልጠናው በቂ ዕውቀትና ክሂሎት ያገኙበት ሲሆን፣ የሥልጠና ሠጣጡም የገጽ ለገጽና በሞዱዩል የታገዘ በመሆኑ ውጤታማ እንደነበር ለመረዳት መቻሉን ሊቀመንበሯ ተናግረዋል።
ሠልጣኞቹ ከአመራርነት ክህሎት በተጨማሪ የባንክ ቢዝነስ (አሠራር) ላይ ያተኮረና ጥልቀት ያለው ሥልጠና
በማግኘታቸው በግለሰብ ደረጃ በልበሙሉነት በየትኛውም መድረክ ዕውቀታቸውን መጠቀም ያስችላቸዋል ብለዋል።

በሥነሥርዓቱ ላይ የፓነል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ በውይይቱም አሠልጣኞችና በባንክ ሥራ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አንጋፎች ልምዳቸውን አካፍለዋል። ሠልጣኞችም በሥልጠናው ወቅት ስላገኙት ዕውቀትና ክህሎት አስረድተዋል።

ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁ ሠልጣኞች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ እጅ ሠርተፊኬት ተቀብለዋል። ለሥልጠናው ስኬት የተለያየ ድጋፍ ያደረጉ አካላት ዕውቅና ተሠጥቷቸዋል።

More from newfin's news